በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የቤተ ክርስቲያን ቅድስናና በቤተ ክርስቲያን አማካይነት የሚሰጠው የእያንዳንዱ ክርስቲያን ቅድስና፤ ከዚያም በላይ በሹመት፥ በምርጫ የሚሰጠው የአበው፤ እንዲሁም በገድል፥ በትሩፋትና በሰማዕትነት የሚሰጠው የብፁዓን ቅድስና፤ «እግዚአብሔር ቅዱስ ነው፤ እሱ የቀደሳቸውም ሁሉ ቅዱሳን ናቸው፤» ከሚለው ትምህርት የሚመነጭ በመሆኑ፤ ሹመቱም ሆነ ማዕረጉ የተሰጣቸው አባቶች ለዚያ ያበቃቸውን እምነትና ምግባር ጠብቀው እስከ ተገኙ ድረስ ተቀባይነቱ የሚያከራክር አይደለም።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፤ የእግዚአብሔር ቅድስና፥ የቤተ ክርስቲያን ቅድስና፥ የሃይማኖት ቅድስና ሲደፈር በጉዳዩ መግባትና የሚፈለገውን ግዳጅ መቀበል የክርስቲያን ሁሉ ተግባር ነው። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በላከው መልእክቱ የሚከተለውን ብሎአል። «... እናንተ ግን የእኛን ፍለጋ ተከተሉ፤ እናንተስ መልአክ ስንኳ ከሰማይ ወርዶ እኛ ካስተማርናችሁ ትምህርት ሌላ ቢያስተምራችሁ ውጉዝ ይሁን። አስቀድሜ እንደ ተናገርኩ አሁንም ደግሞ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት ያስተማራችሁ ቢኖር ውጉዝ ይሁን እላለሁ።» (ገላ፤ ም. ፩፥ ፰ – ፱።)
በዚሁ መሠረት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ፤ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፓትርያርክ አባ ጳውሎስና ግብር አበሮቻቸው የሆኑ ጳጳሳትና ካህናት የነባሪቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ትምህርትና ሥርዓት ደፍረው በማስደፈር፥ በመለወጥና በማናወጥ ያደረጉትን የጥፋት እርምጃ በመቃወም፤ ሕገ ቤተ ክርቲያን በሚፈቅደው ሥርዓትና ቅደም ተከተል መሠረት አውግዘው መለየታቸው ይታወቃል። አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተላለፉትን የመጀመሪያ ቃለ ውግዘት ከዚህ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፤ በተከታታይ ያቀረቧቸውን አቤቱታዎችም ከዚህ ውስጥ ገብቶ መመልከት ይቻላል፡፡
ፓትርያርኩና ግበር አበሮቻቸው ባለፉት ፳ ዓመታት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያደረሱት በደልና ውድቀት ለመላው የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንና ለታዛቢዎች ጭምር ግልጽ በመሆኑና የዚህ መልእክት ወቅታዊ ርእስም ባለ መሆኑ ወደ ዝርዝር ጉዳዩ እነደባም፡፡
ከፓትርያርኩ ኅልፈት በኋላ በአሜሪካ ራዲዮ ጣቢያ ቀርበው ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አንድ ሊቀ ጳጳስ ስለ ፓትርያርኩ መልካም ሰውነትና ታላቅነት የማናውቀውን ለማስረዳት ሲቸገሩ፥ ሲጠበቡ ብንሰማም፤ ሟቹ ፓትርያርክ ግን የሠሩትን ሠርተው ማለፋቸው የታወቀ ነው።
ከዚህ በኋላ እኛን ምእመናንን የሚያሳስበን ዋና ነገር ይህ ሳይሆን የቤተ ከርስቲያናችን መጻኢ ዕድል መሆን አለበት ብለን እናምናለን። በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያስተዳድር ዐደራ የተሰጠው ሲኖዶስ በአንድ ሰው አምባ ገነንነት ታፍኖ በእግዚአብሔርና በሰው ተገዥነት መካከል እግር ተወርች ተወጥሮ፥ ይበልጥ ግን ለሰው ተገዥነት ተሸንፎ መኖሩ የዐደባባይ ሀቅ ሲሆን ዛሬ ግን እግዚአብሔር ባወቀ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከወደቀችበት በማንሣት ወደ ነበረ ክብሯ ለመመለስ የሚያስችለውን የዐሥራ አንደኛ ሰዓት የሥራ ድርሻ አግኝቷል። በሌላ በኩልም የሲኖዶሱ አባላት ካረፉት ፓትርያርክ ጋር የጥፋትና የዐመፃ ተባባሪ እንደ መሆናቸው መጠን ከውግዘት ላይ ወድቀዋልና፤ አሁን ባለው ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኒቱንና ምእመናንን ለመምራት የማይችሉ መሆናቸው፤ ከእነሱም መሓከል በእውነተኛ እምነት ጸንቶ ምእመናንን ሊጠብቅ ይችላል ተብሎ እምነት የሚጣልበት ተተኪ ፓትርያርክ ማግኘት አዳጋች እንደ ሆነ እሙን ነው። ስለ ሆነም የሲኖዶሱ አባላት ቀጣይ ተግባራትን ከማከናወናቸው በፊት፤ ከዚህ በፊት ያጠፉትን ጥፋት በይፋ አምነውና ንስሐ ገብተው፤ ባለፉት ፳ ዓመታት የተበረዙትን የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት አቃንተው፤ ከዐመፅና ከጥፋት ሥራ ርቀው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ጥሪአችንን እናስተላልፋለን። ስለ ሆነም ሲኖዶሱ፤ ለሰው ሳይል ለእግዚአብሔር አድልቶ፤ የምእመናንን የዘመናት ኀዝንና የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እነዲጠግን፤ በልጁ ደም በተቤዠን በኀያሉ አምላክ በእግዚአብሔር ስም እንማጸናለን።
መላ ሕዝበ ክርስቲያንም የዚህ ታሪካዊ ወቅትና የቤተ ክርስቲያን ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ፤ ከተለያዩ ምንጮች በሚወጡ አሉባልታዎች ሳይደናገጥ፤ የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከል ድረስ በትዕግሥት እንዲጸና፤ እንዲሁም ለክርስቲያናዊ መብቱና ነጻነቱ መከበር ተገቢውን ጥረትና ጸሎት እንዲያደርግ እንማጸናለን።
ይህን ዐሳባችንን ያግዝ ዘንድ፤ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ፤ «የእግዚአብሔር ሥርዓት ከሚዛባ የሰው ፈቃድ መለወጥ አለበት፤» በሚል ርእስ ግንቦት ፲፬ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም. በጦማር ጋዜጣ አማካይነት ለሕዝበ ክርስቲያን ያስተላለፉት መልእክት ለወቅቱ ሁኔታ የሚመጥን ሆኖ ስላገኘነው እንድታነቡት አቅርበንላችኋል። መልእክቱን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ፡፡